Tuesday, September 7, 2021

ሃሳብመንግሥትነትን በዝርፊያ አጣችሁት፤ ይኼው አመል ቢያንስ ሽፍታ ሆኖ መኖርን እንኳን ሊነሳችሁ ነው!

መንግሥትነትን በዝርፊያ አጣችሁት፤ ይኼው አመል ቢያንስ ሽፍታ ሆኖ መኖርን እንኳን ሊነሳችሁ ነው!

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ዛሬ የተሸሸጋችሁበትና ያምታታችሁት ህዝብ ትናንት ትዝ ብሏችሁ አያውቅም፡፡ በሥልጣን ዘመናችሁ ከመቀሌ ይልቅ ታይላንድ በአስረሽ ምቺው ከርማችሁ ለስካርና ለዝሙት የሚሆን ብር ሲነጥፍ ወገኔ ብላችሁ ትግራይ ገባችሁ፡፡

ክብርና ስልጣን ነበራችሁ፤ ግን ያልዘረፋችሁት ነገር የለም፡፡ ከመሬት ተነስተው ቢሊየነር ስለሆነ ጄነራሎች ንብረት መወረስ ሲነገር እንኳን “ከየት አመጡት?” ከሚለው ይልቅ “የተጋሩ ጥቃት” እያለ የሚያወራው ግልብ ደጋፊ አስክሯችሁ ሀገር አወደማችሁ፡፡

እኛ ያልተደረገንነው ምንድን ነው? ደርግን ጣልን ብላችሁ ስትገቡም ዘርፋችሁናል፤ ለውጥ ተቀብለናል ብላችሁ ስትወጡም ዘርፋችሁናል፡፡ አናሳ ሆናችሁ እኩል እንሁን እንኳን ስንል እንደ ድፍረት ቆጥራችሁ የብሔር ጥላቻን በመስበክ የተበታተነች ሀገር ለመፍጠር ደክማችኋል፡፡

መንግስት ነበራችሁ፤ ግን ሌብነትን ክብር ሰጥቶ ካልተያዘ ችግር የለውም በሚል መሪ የሚመራ መንግስት፤ ወታደር ነበራችሁ ግን ያለ እረፍት ኮንትሮባንድ በመነገድ ለሚሊዮኖች ስደትና ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆናችሁ ታጋዮች፡፡

ያካበታችሁትን ልባችሁ ያውቀዋል፤ የዘረፋችሁትም እንዲሁ ታውቁታላችሁ፡፡ አዲስ አበባን አይቶ የማያውቅ የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም እጣ ወጣልኝ ብሎ የሚመጣባትን ዋና ከተማ ምን እንዳደረጋችኋት ልባችሁ ያውቃል፡፡

ኢትዮጵያውያን ላይ መድረቅ ይቻል ይሆናል ግን ልቦናችሁ የማይክደው ጸሐይ የሞቀውና ሀገር ያወቀው ብዙ ጉድ ነበር፤ ብዙ ግፍና መከራ ስቃይ እና ስቆቃ ከአስከፊ ዝርፊያና ሌብነታችሁ ጋር ተዳምሮ መንግስትነትን አጣችሁ፡፡

ሀገር ባንመራስ ክልል ብንመራስ ብላችሁ በገባችሁበት የመቀሌ መሰባሰብ ዘመናችሁም እንዲሁ የኢትዮጵያ እልቂት ሞትና መከራ ድግስ ደጋሾች ሆናችሁ፤ ዝርፊያውና ሌብነቱ ቀጠለ፤ እንደ አራት ኪሎው መቀሌን ለቃችሁ ዋሻ ከተታችሁ፤
ደግሞ ሽፍታና ነጻ አውጪ ነን ብላችሁ ትግል ስትጀምሩ ዳግም ሌብነት መርሃችሁ ይሆናል ብሎ የገመተ የለም፡፡ መርከብ ከመስረቅ ወደ ሊጥ ይዞ ሽሽት ይገባል ብሎ ማንስ ሊያስብ ይችላል?

የትግል ታሪካችሁ ሁለት ነባር እሴቶች ቆረጣና ዝርፊያ እንደሆነ ዳግም በታሪክ ፊት ለአዲስ ትውልድ አረጋገጣችሁ፡፡ ሀገር ዘርፋችኋል ብሎ ይጠላችሁ የነበረን ገበሬ ጎጆ ዘረፋችሁ፤ ሌባ ናችሁ ስትባሉ የሚሽኮረመሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መጋዘን ሳይቀር መዘበራችሁ፡፡

ይሄ ዝርፊያ ውድመትና ስቆቃ ምናልባትም ሀገርን አንድ አድርጎ በአንድ አላማ አሰለፈ እንጂ የትግሉን ጥንካሬ አልቀየረውም፡፡ ኢትዮጵያ እንዳትዘርፏት፣ እንዳትገድሏትና እንዳታፈርሷት በጽናት ከዳር ዳር ቆማለች፡፡

ትናንት ትጠየፉት የነበረውን የትግራይ ህዝብ ዛሬ መሸሸጊያ አድርጋችሁ ቢወልዳችሁ አምኗችሁ ወደ ከፋ ስቃይና መከራ እየገባ መሆኑ አያሳስባችሁም፡፡ እናንተ ከምትመሩት ህዝብ ይልቅ አንድ መለኪያ ውስኪ የሚበልጥባችሁ ጨካኞች ስለሆናችሁ ድል አደረገን ብላችሁ የታማኝ በየነን ቤተሰብ እንዲያ ስታሰቃዩ በአጻፋው የእኛ ቤተሰብ እንዲህ ያለ ነገር ቢገጥመውስ የሚለው አያሳስባችሁም፡፡ ንጹሃን የሚለው ቃል የፖለቲካ መነገጃችሁ እንጂ መርሃችሁ አይደለም፡፡

ለገዛ እናቱ የማያስብ እና በገዛ እናቴም ቢመጡብኝ ደስታዬ እጥፍ ነው የሚል ሀሺሻም ለገዛ ሀገሩ ያስባል ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ግን ለሀገሩ የሚያስብ ሀገሩን የሚያድን ለሀገሩ የሚሆን መቶ ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡

https://news.et/2021/09/04/%e1%88%98%e1%8a%95%e1%8c%8d%e1%88%a5%e1%89%b5%e1%8a%90%e1%89%b5%e1%8a%95-%e1%89%a0%e1%8b%9d%e1%88%ad%e1%8d%8a%e1%8b%ab-%e1%8a%a0%e1%8c%a3%e1%89%bd%e1%88%81%e1%89%b5%e1%8d%a4-%e1%8b%ad%e1%8a%bc/

Friday, December 27, 2019

በሞጣ ከተማ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰው ጥቃት እየተወገዘ ነው

በሞጣ ከተማ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰው ጥቃት እየተወገዘ ነው

በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ ዓርብ ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ፣ በቤተ ክርስቲያንና በመስጊዶች ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጥቃት በመላ አገሪቱ እየተወገዘ ነው፡፡
የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያው በሆነው በጥንታዊውና ታሪካዊው ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የእሳት ቃጠሎ ሙከራ መደረጉ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ መስጊዶችና ሱቆች መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡
ድርጊቱ የሁለቱንም ሃይማኖት ተከታዮች የማይወክልና ለዘመናት በአካባቢውና በዙሪያው በፍቅር ያሳለፉትን ጊዜ የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን፣ በክርስቲያንና በሙስሊም ማኅበረሰቦች እየተወገዘ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ጭስ በመታየቱ የአካባቢው ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በፍጥነት ተረባርበው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉ አስደሳች ቢሆንም፣ ስሜትን አስቀድመው ይሁን ወይም ሌላ ተልዕኮ ተቀብለው በማይታወቅ ሁኔታ መስጊዶችንና ሱቆችን ያቃጠሉና የዘረፉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ እንዲቀርቡ የሁለቱም እምነት ተከታዮች እየጠየቁ ነው፡፡
ለበርካታ ዘመናት ጠንካራ ትስስር ያለው የሞጣ ሙስሊምና ክርስቲያን፣ በጊዜ አመጣሽ የውንብድና ሥራ የሚፈታ እንዳልሆነ ማሳያው ሰሞኑን በሁለቱም በኩል እየተደረገ ያለው የእርስ በርስ መደጋገፍ ዓይነተኛ ምስክር መሆኑን በርካታ የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ሙስሊሙ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ክርስቲያኑ መስጊዶችን ላለፉት ሺሕ ዓመታት እየገነቡና እየተጋገዙ እንደኖሩት ሁሉ፣ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውና የክልሉ መንግሥት የተቃጠሉትን እንደሚገነቡም እየተገለጸ ነው፡፡
በእምነት ተቋማት ላይ የሚደረግ ጥቃት መወገዝ እንዳለበት የሚናገሩት ነዋሪዎች ሰሞኑን በሞጣ አንድ መስጊድ ውስጥ የተያዘ አንገቱ ላይ ማተብ ያሰረ ወጣት፣ በድጋሚ ጥቃት ለማድረስ ሳይሆን ሆን ብሎ የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች ትስስር ለማለያየት የተደረገ ሙከራ በመሆኑ መንግሥት ተጠርጣሪውን በደንብ መርምሮ ሥረ መሠረቱን ማወቅና ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት በክልሉ በሚገኙ የእምነት ተቋማት፣ የትምህርትና የንግድ ተቋማት ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሱት ጥቃቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ የነዋሪዎችን ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦች ላይ ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠይቋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ቦርድ ሰብሳቢ መልአከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፣ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ሰይድ አህመድ፣ የክልሉ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃምና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን ቤተ እምነቶች ጎብኝተዋል፡፡ መስጅዶቹን ለመሥራትም ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ይኼ ነገር ባይፈጠር መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ተፈጥሯል፡፡ ልባችንን የሚነካ ክስተት ነው፡፡ ምናልባትም አላህ የተሻሉ ሆነው መስጅዶቻችን እንዲሠሩ ፈልጎ ይሆናል፡፡ አላህ በሰበብ አስባብ አይደል የሚያደርገው፤›› ያሉት ቀዳሚ ሙፍቲ ዑመር እንድሪስ ሲሆኑ፣ ‹‹ባለሥልጣኖቻችን ለሥልጣን ሲሉ በሕዝቡ ላይ መርዝ ነሰነሱበት እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ መስጊዶች በአማራ ክልል  ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክልሎች የተቃጠሉ ቢሆንም፣ ድርጊቱ ግን ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን እንደማይወክል በርካታ የሁለቱም እምነት ተከታዮች ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ሕግ በማስከበር መስክ ከፍተኛ ድክመት እየታየበት መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ጥቃት አድራሾቹን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተፈጸሙ አሳፋሪ ድጊቶችም እንዳይደገሙ ቁጥጥሩን ያጥብቅ ብለዋል፡፡ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት ሹሞች ተጠያቂ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com/article/17645

Saturday, December 21, 2019

የሰላም የኖቤል ሽልማቱ ትሩፋትና ዕዳ



የሰላም የኖቤል ሽልማቱ ትሩፋትና ዕዳ

ባለፈው ሳምንት ታላላቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከበጎ ሥራዎችና ስኬቶች ጋር በማቆራኘት፣ የዘገባቸው ማሟሻና የትንታኔያቸው ማሳያ አድርገው ሰንብተዋል፡፡
ፍረወይኒ መብራሃቱ የሲኤንኤን የዓመቱ ጀግኒት መሆኗን በመዘገብና በማብራራት ላይ እያሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኖቤል የሰላም ሽልማትን መቀበል አክለውበት የመገናኛ ብዙኃኑ ስለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዘግበዋል፣ እየዘገቡም ነው፡፡
በተለይ ማክሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ ርዕሰ ከተማ ኦስሎ ተገኝተው የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን በተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ከሽልማቱ ጋር በተገናኘ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡
የተለያዩ የማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ያሉ ኢትዮጵያውንም ከኖቤል የሰላም ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ፣ በተለየ መንገድ ተቃውሞ ያሰሙ ጥቂቶችም ተስተውለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ለሰላም ያላቸውን ቀናዒነት በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ወጣት ወታደር በነበሩበት ወቅት የጦርነትን አስከፊ ገጽታ የተመለከቱ በመሆናቸው ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነገር እንደሆነና ሁሉም ተረባርቦ ሊያረጋገጠው የሚገባ እጀግ ውድ ዋጋ ያለው ሀብት መሆኑን በአጽንኦት ሲከታተሉዋቸው ለነበሩ ሁሉ አስረድተዋል፡፡
በተለይ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በወጣት ዕድሜያቸው በራዲዮ ኦፕሬተርነት በተሳተፉበት ወቅት በጓዶቻቸው ላይ የደረሰውን ጥቃትና ዕልቂት አስታውሰው፣ በወቅቱ የተሰው ጓዶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሁሌም እንደሚያስቧቸው ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በጦርነት መሀል ሆነው መታዘባቸው፣ ለሰላም ጠንክረው እንዲሠሩ ገፊ ምክንያት እንደሆናቸውም አብራርተዋል፡፡
ከአሥራ ስምንት ወራት በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ቅድሚያ ሰጥተው ካከናወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነትም ሰላምም የሌለበትን ፍጥጫ በመቅረፍ በሁለቱ አገሮች መሀል ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነበር፡፡
ይህ የሰላምና የዕርቅ ውሳኔና ጥሪ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ በማግኘቱና በሁለቱ አገሮች መካከል ተቋርጠው የነበሩት የአየር ትራንስፖርትና የቴሌኮም አገልግሎት የተጀመሩ ሲሆን፣ ለዓመታት ተዘግተው የነበሩ ድንበሮች ለጥቂት ወራትም ቢሆን ተከፍተው ነበር፡፡
ይህን በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ የተፈጠረውን ለውጥ በዋነኛነት ከግምት ያስገባው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የዘንድሮ የሰላም ተሸላሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሽልማታቸውን በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተቀብለዋል፡፡ ከሽልማቱ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው፡፡ አብዛኞቹ አስተያየቶች አዎንታዊ ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል ያለው ወቅታዊ ግንኙነትን በማውሳት አሉታዊ አስተያየቶች የሰጡም አሉ፡፡
በተለይ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት አሁን ላይ በጀመረው ፍጥነት መጓዝ ባለመቻሉ፣ የድንበሮቹ መልሶ መዘጋት፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አለመሆንና ተቋማዊ አሠራር አለመዘርጋቱን በመጥቀስ የሽልማቱ ተቺዎች የሚሰጡት አስተያየት ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በቅርብ ዓመታት መፍትሔ ያገኛል ተብሎ የማይገመተውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በምንም ሁኔታ ቢሆን ወደ ሰላም ማምጣታቸው በራሱ ትልቅ ስኬት ነው በማለት፣ ሽልማቱና ዕውቅናው ተገቢ እንደሆነ የሚሟገቱ አሉ፡፡  
 የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴም ቢሆን ሽልማቱን ለእሳቸው ለመስጠት ሲወስን ወቅታዊውን ሁኔታ አይገነዘብም ብሎ ማሰብ እንደሚያስቸግር የሚገልጹ ወገኖች፣ ሽልማቱ ያላቸውን ተነሳሽነትና ቀጣይ ቀጣናዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የተሰጠ ተገቢ ዕውቅና እንደሆነም፣ ለመከራከሪያቸው ማጠናከሪያ አድርገው ያቀርቡታል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በሽልማቱ ወቅት ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝን ለመመከት ያሳየችው ቀደምት ተጋድሎ፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ከመድረኩ መሰማቱ ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውን እንደሆነ በመግለጽ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ይሞግታሉ፡፡
ከኖቤል የሰላም ሽልማት መረጣና ዕውቅና ጋር በተገናኘ የተጻፉ በርካታ መጣጥፎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ፣ ሽልማቱን የሚቀበሉ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ ተቃውሞዎችን ማስተናገዳቸው የተለመደ ነገር እንደሆነ ያወሳሉ፡፡
አንዳንድ ጽሑፎች ሽልማቱን ፖለቲካዊ አንድምታው የጎላ በመሆኑና ፖለቲካ ደግሞ የተለያየ አረዳድ፣ ትንተና፣ እንዲሁም ትርጉም የሚሰጠው ከመሆኑ አንፃር ሽልማቱ ማጨቃጨቁ አይቀሬ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
እንደ ማሳያነትም የመጀመርያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሰላም ሽልማት አሸናፊ በሆኑበት ወቅት የተነሳውን ተቃውሞና ጭቅጭቅ የሚያቀርቡ በርካቶች ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ለሰላም ኖቤል አሸናፊነት የተመረጡት ምንም ሳይሠሩና የፕሬዚዳንትነት አገልግሎታቸውም አለመፈተኑን በመጥቀስ በወቅቱ ከፍተኛ ትችት ይሰነዘሩ እንደነበሩት ሁሉ፣ ፕሬዚዳንቱ ለዓለም ሰላም በትጋት እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም ከነበራቸው ተቀባይነትና የለውጥ ወኪልነት አንፃር፣ ለዓለም ሰላም ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት የተሰጣቸው ዕውቅና ተገቢ ነው በማለት የሚሞግቱ በርካቶች ነበሩ፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም፣ እንዲህ ከመሰሉ ክርክሮች ሊያመልጡ እንደማይችሉ ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታና ትንታኔ መረዳት ይቻላል፡፡
በዚህም ምክንያት በተለይ በርከት ያሉ ኤርትራውያን እንደ አልጄዚራና ሲኤንኤን በመሳሰሉ መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ዜጎች ላይ እየደረሳቸው ያሉ በርካታ ጉዳዮች በመዘርዘር ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፣ በኦስሎ ከተማ ተገኝተውም የተቃውሞ ሠልፍ አድርገዋል፡፡
ነገር ግን ለእነዚህ ግለሰቦች በርካታ ኢትዮጵያውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኤርትራ የውስጥ ጉዳይ የኤርትራውያን እንጂ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይ አይደለም፣ ሽልማቱም የተሰጠው በሁለቱ አገሮች ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት በማደሳቸው እንጂ፣ ኤርትራውያኑ የሚያነሱትን የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደራዊ ጥያቄ እንዲፈቱ በማድረጋቸው አይደለም በማለት፣ ለተቃውሞው ምላሽ በመስጠት ተጠምደው ሰንብተዋል፡፡
ሌላው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከሽልማቱ በኋላ ሲሰነዘሩ የነበሩ አስተያየቶች ደግሞ ሽልማቱ ተገቢ መሆኑን የሚጠቅሱ ቢሆኑም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽልማቱንና የዕውቅናውን ያህል በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋለውን የሰላም ዕጦት በመቅረፍ፣ በመላ አገሪቱ መረጋጋት በማስፈን የሰላም አባትነታቸውን ማስመስከርና ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የሚወተውቱ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ውትወታ በተጨማሪም፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንም ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ዘርፍ ተግተው እንዲሠሩ በር የሚከፍት ዕውቅና እንደሆነ ከመግለጽ ባለፈ፣ ሰላምን በመላ አገሪቱ ለማስፈንና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ አለመረጋጋቶችን ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አንፃር ከፍተኛ ሥራ የሚጠብቃቸው ከመሆኑ አንፃር ሽልማቱ አብሮ ይዞት የመጣው ዕውቅና ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑንም በዘገባቸው አንፀባርቀዋል፡፡
የሰላም የኖቤል ሽልማት መሰጠት የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ1901 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ 100ኛ የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ከአፍሪካ ተሸላሚዎች ተርታ ተሠልፈዋል፡፡
የኖቤል ሽልማት መርሐ ግብሮች ሰላም፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ እንዲሁም የሳይንስ ዘርፎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በእስካሁኑ የሽልማት ሥነ ሥርዓትም ለ597 ጊዜያት ያህል በተካሄዱ የሽልማት ሥነ ሥርዓቶች ለ950 ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማቱ ተበርክቷል፡፡
ከአፍሪካ የሰላም የኖቤል ሽልማትን እ.ኤ.አ. በ1960 በመቀበል ደቡብ አፍሪካዊ መምህር፣ ወትዋችና ፖለቲከኛ የነበሩት የአፍሪካን ብሔራዊ ኮንፈረንስ (ANC) ፕሬዚዳንት የነበሩት አልበርት ሉቱሊ ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ከእሳቸው ቀጥሎ በርካታ አፍሪካውያን ሽልማቱንና ዕውቅናውን አግኝተዋል፡፡
የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተቀበሉ ሌሎች አፍሪካውያን ደግሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት፣ በእስራኤልና በግብፅ መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ላሳዩት የሰላም መነሳሳት ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ሜናሂም ቤጊን ጋር እ.ኤ.አ. በ1978 በጋራ ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት ባደረጉት አስተዋጽኦ እንዲሁ በ1984 ዓ.ም. የኖቤል ሽልማት ለቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ የተበረከተ ሲሆን፣ ሌላው ደቡብ አፍሪካዊ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በ1993 ዓ.ም. ከፌሬደሪክ ዴክለርክ ጋር ሽልማቱን ወስደዋል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪም ጋናዊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን በ2001 ዓ.ም.፣ ኬንያዊቷ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ዋነጋራ ማታይ በ2004 ዓ.ም.፣ ግብፃዊው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ዳይሬክተር የነበሩት መሐመድ አልባራዳይ በ2005 ዓ.ም.፣ የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ በ2011 ዓ.ም.፣ እንዲሁም የፀደይ አብዮትን ተከትሎ በቱኒዝያ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ለመፍታት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የቱኒዝያ ናሽናል ዲያሎግ ኳርቴት እንደ ተቋም ሽልማቱን በመውሰድ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም እዚህን አፍሪካውንን የሰላም ሽልማቱን በመቀበል የተቀላቀሉ ሲሆን፣ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የሽልማቱን በረከት ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየር እንደ መነሻ እንደሚሆንና ያላቸውን የሰላም ቀናዒነት ማረጋገጫ ማኅተም ተደርጎ ይወስድ ዘንድ፣ በመላ አገሪቱ ሰላምን ማስፈን ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው በርካቶች ያስረዳሉ፡፡
https://www.ethiopianreporter.com/article/17572